1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የወሰደው እርምጃ ለውጥ እያመጣ ነው?

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ግንቦት 7 2016

የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት በሚያዝያ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 23.3% ሆኖ መመዝገቡን አስታውቋል። የታየውን ለውጥ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ “ታላቅ ዕምርታ” ብለውታል። የምግብ ነክ ዕቃዎች የዋጋ ግሽበት ግን 27% ሆኖ ተመዝግቧል። ዳቦ እና ጥራጥሬን የመሳሰሉ ምግቦች ከ2015 ሚያዝያ አኳያ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል።

https://p.dw.com/p/4ftkC
ደብረ ማርቆስ ገበያ
በኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ መሠረት ምግብ ነክ የዋጋ ግሽበት በሚያዝያ ወር 27 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።ምስል DW/E. Bekele

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የወሰደው እርምጃ ለውጥ እያመጣ ነው?

የሚያዝያ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 23.3 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ይፋ አድርጓል። መንግሥታዊው ተቋም ይፋ ያደረገው አሀዝ ከቀደመው መጋቢት ወርም ሆነ ከ2015 ተመሳሳይ ጊዜ አኳያ የዋጋ ግሽበት የሚያድግበት ፍጥነት የመቀነስ አዝማሚያ እንዳሳየ የሚጠቁም ነው።

በኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት መረጃ መሠረት ባለፈው መጋቢት ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 26.2 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል። ከአንድ ዓመት በፊት ማለትም በሚያዝያ 2015 በአንጻሩ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 33.5 በመቶ ነበር።

“ባለፈው ዓመት የነበረው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 33.5 በመቶ ነበር” ያሉት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ ባለፈው ሣምንት ኢትዮጵያ ታምርት በተባለው ንቅናቄ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር “በአሁኑ ጊዜ ወደ 23.3 በመቶ ቀንሷል። ስለዚህ በ10.2 በመቶ ቀንሷል። ይኸ ትልቅ ዕምርታ አድርገን ነው የምንወስደው” ሲሉ ተደምጠዋል

አቶ ማሞ የሚመሩት ብሔራዊ ባንክ በነሐሴ 2015 ሥራ ላይ ባዋላቸው መመሪያዎች እና የፖሊሲ እርምጃዎች የዋጋ ግሽበትን በመጪው ሰኔ ከ20 በመቶ በታች የማውረድ ዕቅድ አለው።

ባደጉት ሀገሮች የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ የሚቀመጠው ግብ ግልጽ እንደሆነ የሚናገሩት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ “የብሔራዊ ባንክ ከ20 በመቶ በታች ስላለ በጣም አስቸጋሪ ነው። 18፣ 17፣ 16…አይታወቅም” ሲሉ ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ “ባለፈው ዓመት የነበረው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 33.5 በመቶ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ወደ 23.3 በመቶ ቀንሷል። ስለዚህ በ10.2 በመቶ ቀንሷል። ይኸ ትልቅ ዕምርታ አድርገን ነው የምንወስደው” ሲሉ ተደምጠዋልምስል CC BY 2.0/U.S. Institute of Peace

የዋጋ ግሽበት በ19.9 በመቶ እንኳ ቢወርድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕቅዱን “አሳክቻለሁ ሊል ይችላል” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን የታየው ለውጥ ወደ ዕቅዱ የሚመራ ቢሆንም ብዙ እንደሚቀር አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕቅድ በነሐሴ 2015 ይፋ የሆነው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት ከዋጋ ግሽበት በተጨማሪ የበጀት ጉድለት፣ የገቢ እና ወጪ ንግድ ሚዛን መዛባት በመሳሰሉ ሥር የሰደዱ ፈተናዎች በተቸገረበት ወቅት ነው።

ዕቅዱን ለማሳካት ብሔራዊ ባንክ ይወስዳቸዋል ከተባሉ እርምጃዎች መካከል ለመንግሥት የሚሰጠውን የቀጥታ ብድር በመቀነስ ከ2015 አኳያ “ከሲሶ (ከ1/3ኛ) እንዳይበልጥ” መገደብ ይገኝበታል። ይሁንና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሪፖርቱን በወቅቱ ለሕዝብ ይፋ ባለማድረጉ ቃል በገባው መሠረት ለመንግሥት የሚሰጠውን ብድር መገደቡን ማረጋገጥ እንደማይቻል ዶክተር አብዱልመናን ገልጸዋል።

ብሔራዊ ባንክ በገበያው ውስጥ የሚዘዋወረውን የገንዘብ መጠን በመቀነስ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ሲነሳ የተከተለው ሌላው እርምጃ ባንኮች የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ ያነጣጠረ ነው።

የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ባንኮች የሚሰጡት ብድር ባለፈው ዓመት ካቀረቡት ከ14 በመቶ እንዳይበልጥ ገድቧል። ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሲያጋጥማቸው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለሚወስዱት የአስቸኳይ ጊዜ ብድር የሚከፍሉት ወለድ “ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ” ብሏል።

የኢትዮጵያ ብር እና ሽንኩርት በመደብር
ከ2015 ሚያዝያ ወር አኳያ ዳቦ እና ጥራጥሬ የ35.3 በመቶ፣ አትክልቶች የ34.2 በመቶ፣ የሥጋ 25.2 በመቶ  የዋጋ ጭማሪ ታይቶባቸዋል።ምስል Eshete Bekele/DW

በሚያዝያ 2016 አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 23.3 በመቶ ሆኖ የተመዘገበው የገንዘብ አቅርቦት ዕድገትን ለመግታት በተወሰደው እርምጃ ምክንያት እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ቅዳሜ ባሠራጨው መረጃ አስታውቋል።

ላለፉት ዘጠኝ ወራት ገደማ ብሔራዊ ባንክ የተከተለው እርምጃ የዋጋ ግሽበትን በ2017 ሰኔ ወር ከ10 በመቶ በታች ለማውረድ ጭምር የተወጠነ ነው። አቶ ማሞ ምኅረቱ ባለፈው ሣምንት “ኢትዮጵያ ታምርት” በተባለው ንቅናቄ መድረክ ላይ ተገኝተው ሲናገሩ በዋጋ ግሽበት ላይ የታየው ለውጥ ብሔራዊ ባንክ የወሰዳቸው እርምጃዎች ውጤት እንደሆነ ገልጸዋል።

ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕቃዎች የዋጋ ግሽበት ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረበት 36 በመቶ ወደ 18 በመቶ ዝቅ ማለቱን የጠቀሱት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይኸም የመንግሥታቸው “የተጠናከረ እና የተቀናጀ እርምጃ” ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።

“ያሰብንውን አሳክተናል ብለን ነው የምንወስደው” ያሉት የብሔራዊ ባንክ ገዥ “በተለይ core inflation ላይ የሞነተሪ ፖሊሲ ውሳኔያችን ግልጽ የሆነ ውጤት አምጥቷል ብለን እናምናለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

በዋጋ ግሽበት ላይ የታየው ለውጥ ለብሔራዊ ባንክ አዎንታዊ ትርጉም የሰጠ ቢሆንም ሸማቾች ግን የተለየ ፋታ የሚያገኙበት አይደለም። የዋጋ ግሽበት የሚገኝበትን ደረጃ ለማወቅ የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ሲሰራ የናሙና አወሳሰድ፣ የሚሰላበት መንገድ እና ትንታኔው ሸማቾች በለት ተለት ግብይት የሚገጥማቸውን ያሳያል ወይ የሚለው ጉዳይ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።

በኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ መሠረት ምግብ ነክ የዋጋ ግሽበት በሚያዝያ ወር 27 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል። ከ2015 ሚያዝያ ወር አኳያ ዳቦ እና ጥራጥሬ 35.3 በመቶ፣ አትክልቶች 34.2 በመቶ፣ ሥጋ 25.2 በመቶ  የዋጋ ጭማሪ ታይቶባቸዋል።

ወተት፣ አይብ እና እንቁላል የመሳሰሉ የምግብ ግብዓቶች የመሸጫ ዋጋ 18.3 በመቶ ሲጨምር ዘይት 12.2 በመቶ፣ ፍራፍሬ 6.7 በመቶ እንዲሁም የምግብ ምርቶች 21.6 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል።

የዋጋ ግሽበት የሚቀንስበት ፍጥነት “በጣም በዝግታ ነው” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን ለውጡ በአፋጣኝ በሸማቾች ላይ የሚንጸባረቅ እንዳልሆነ ያስረዳሉ።

“ሸማች ሊመገባቸው የሚችላቸው ወይም ወጪ ሊያወጣባቸው የሚችላቸው ነገሮች ይደመሩና በዚያ ላይ ተመርኩዞ [የዋጋ ግሽበት ምጣኔ] ይሰላል” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን የስሌቱ መሠረት የሆነው የምግብ ቅርጫት “ለሁሉም ሰው ላይሠራ ይችላል” ሲሉ እንደ ሰዉ አቅም እና ፎጆታ እንደሚወሰን አስረድተዋል።

የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ብሔራዊ ባንክ ገቢራዊ ካደረጋቸው እርምጃዎች መካከል ባንኮች የሚያቀርቡትን ብድር ለመገደብ የተላለፈው ውሳኔ በአዲስ አበባ የሪል ስቴት ገበያን ሲያንገጫግጭ ታይቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
በሚያዝያ 2016 አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 23.3 በመቶ ሆኖ የተመዘገበው የገንዘብ አቅርቦት ዕድገትን ለመግታት በተወሰደው እርምጃ ምክንያት እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ቅዳሜ ባሠራጨው መረጃ አስታውቋል።ምስል Eshete Bekele/DW

ባንኮች የሚሰጡት ብድር ላይ በተጣለው ገደብ ምክንያት በሪል ስቴት ገበያ የገዢዎች ፍላጎት የተቀዛቀዘ ሲሆን የመሸጫ ዋጋም የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቷል።

“በተለይ በአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤት ዋጋ እንዲጨምር ያደረገው ከባንክ የሚገኝ መጠነ ሰፊ ብድር ነው” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “ነጋዴዎች ለንግድ ብለው ብድር ይወስዳሉ፤ ወደ ሪል ስቴት ያውሉታል። ያ ገንዘብ ደግሞ የመኖሪያ ቤትን ዋጋ እያናረው መጣ” ብለዋል።

የሀገሪቱ ትልልቅ ኩባንያዎች በዋንኛነት የከተሙበት የአዲስ አበባ የሪል ስቴት ገበያ ባለፉት ዓመታት በገዢዎች ፍላጎት እና የመሸጫ ዋጋ ዕድገት ሲታይበት ቆይቷል።

ባንኮች ሲያቀርቡት ከቆዩት ከፍ ያለ ብድር በተጨማሪ በተለያዩ ምክንያቶች ዋና ከተማዋ የሀገሪቱ ዜጎች ተመራጭ ማረፊያ መሆኗ የመኖሪያ ቤቶች የመሸጫ ዋጋ በአዲስ አበባ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ካደረጉ ምክንያቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ዘርፉ የከተማዋን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት መሙላት ባይችልም የዕድገቱ ዘላቂነት በበርካታ ባለሙያዎች ጥያቄ የሚነሳበት ሆኖ ቆይቷል።

“የአሴት ዋጋ እና የገንዘብ አቅርቦት (ብድር) በየትኛውም ዓለም በቀጥታ የተገናኙ ነገሮች ናቸው” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን ብሔራዊ ባንኮች ብድር በከፍተኛ መጠን እንዲቀርብ ሲፈቅዱ የመኖሪያ ቤት ዋጋ እንደሚጨምር ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን የመሳሰሉ ተቋማት ቆንጠጥ ያለ የገንዘብ ፖሊሲ መከተል ሲጀምሩ በአንጻሩ የመኖሪያ ቤት የመሸጫ ዋጋ ይቀንሳል። በኢትዮጵያም የሆነው ተመሳሳይ እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር አብዱልመናን “አሁን ብድር በገፍ አይገኝም። በገፍ ብድር ስለማይገኝ ግንባታውም ተቀዛቀዘ ገዢውም የለም” ሲሉ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ