1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት ውሳኔ - የኢትዮጵያ ምላሽ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 24 2016

የአውሮጳ ኅብረት በአሕጉሩ በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ በተባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ የጣለው ጊዜያዊ የሕጋዊ ሰነድ - ቪዛ ገደብ ርምጃ እንዳሳዘነው የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል ። የኅብረቱ ምክር ቤት ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ላይ ያሳለፈው የቪዛ ገደብ ውሳኔ የማይጠቅም መሆኑን አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/4fR0y
Themenbild Europawahl 2024 | Symbolbild Frau mit EU-Flagge
ምስል Pond5 Images/IMAGO

የአውሮጳ ኅብረት በኢትዮጳያውያን ላይ የጣለው የቪዛ ቁጥጥር

የአውሮጳ ኅብረት በአሕጉሩ በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ በተባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ የጣለው ጊዜያዊ የሕጋዊ ሰነድ - ቪዛ ገደብ ርምጃ እንዳሳዘነው የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል ። ቤልጂየም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የአውሮጳ ሕብረት ይህንን አቋሙን እንዲያጤነው የጠየቀ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ድዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው የሕብረቱ ምክር ቤት ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ላይ ያሳለፈው የቪዛ ገደብ ውሳኔ የማይጠቅም መሆኑን ተናግረዋል ። ከአዲስ አበባ ሰለሞን ሙጬ ዝርዝር ዘገባ አለው ።

ስማቸውን መግለጽ ካልፈለጉ አንድ ምንጭ ባገኘነው መረጃ መሠረት አውሮጳ ውስጥየጥገኝነት ማመልከቻ  አስገብተው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ከታየ በኋላ አውሮፓ ውስጥ መኖር አትችሉም የተባሉ ኢትዮጵያዊያንን ጉዳይ የሚያጣራ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጣ ብሔራዊ ኮሚቴ ተዋቅሮ ነበር። በአሕጉሩ ማመልከቻ አስገብተው ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ከነበሩት ሰዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ ያህሉ ኢትዮጵያውያን ሳይሆኑ መገኘታቸውንም ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያውያኑን ጉዳይ የሚከታተል ብሔራዊ ኮሚቴ ተዋቅሮ ነበር

የአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት በኅብረቱ ሥር ያሉና ለኢትዮጵያውያን ቪዛ ለመስጠት ይውሉ የነበሩ ነባር አሠራሮች ላይ ገደብ ማድረጉን ያስታወቀው አውሮጳ ውስጥ በሕገ ወጥ መልኩ ይኖራሉ የተባሉ ዜጎችን ለመቀበል የኢትዮጵያ መንግሥት አሳየው የተባለው ተባባሪነት አናሳና እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን በመጥቀስ ነው።

ውሳኔው የአውሮጳ ሕብረት አባል በሆኑት ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያዊያን ከአንድ ጊዜ በላይ ወደ ሕብረቱ አባል ሀገራት ገብተው እንዲወጡ የሚያስችላቸውን ቪዛ ማግኘት የሚችሉበትን አሠራር ወይም እድል የሚነፍግ ነው። በውሳኔው መሠረት የዲፕሎማት እና የአገልግሎት ፓስፖርት ያላቸው ኢትዮጵያውያንም ያለ ክፍያ ቪዛ እንዲሰጣቸው ይፈቅድ የነበረው መብት ይነሳል። ከዚህም አልፎ ኢትዮጵያውያን ቪዛ ለማግኘት የሚጠብቁት ጊዜ ከነበረበት 15 የሥራ ቀናት ወደ 45 ከፍ እንዲል አዲሱ ውሳኔ ያስገድዳል።

የጀርመን የስደተኞች እና ፍልሰተኞች የፌዴራል መሥሪያ ቤት
የጀርመን የስደተኞች እና ፍልሰተኞች የፌዴራል መሥሪያ ቤትምስል Christoph Hardt/Geisler-Fotopres/picture alliance

ዶቼ ቬለ ስማቸውም ፣ ድምፃቸውም አየር ላይ እንዳይውል ከጠየቁ አንድ የዲፕሎማቲክ ምንጭ ባገኘው መረጃ እንደተረዳው ከሆነ ግን "የተለያዩ መሥሪያ ቤቶችን ያካተተ ብሔራዊ ኮሚቴ ተዋቅሮ በአውርፓ ሕገ ወጥ ሊባሉ የማይችሉ" ዜጎችን ጉዳይ የሚከታተል ቡድን ወደ ዚያው ተጉዞ ነበር።

ቡድኑ "የጥገኝነትመመልከቻ አስገብተው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ታይቶ፣ በአውሮጳ ውስጥ መኖር አትችሉም የተባሉ ኢትዮጵያዊያንን ጉዳይ ሊያጣራ" የተጋዘ መሆኑንም ለማወቅ ችለናል።

እኒሁ ሰው አክለውም በሕብረቱ ሕገ ወጥ ከተባሉት መካከል "ከግማሽ ያህሉ በላይ ኢትዮጵያውያን ሳይሆኑ ነው የተገኙት" ብለዋል። "ቡድኑ ይሄን ሁሉ ሂደት ሠርቶ ኢትዮጵያዊያኖችንም አነጋግሮ በቀጣይ የጉዞ ሰነድ ተዘጋጅቶላቸው እንዲመለሱ የሚደረግበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት ነው ይህ የምክር ቤቱ መግለጫ የወጣው"። ሲሉም ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

"የኢትዮጵያ መንግሥትም ሰዎቹ ለተሻለ ኑሮ የወጡ እስከሆኑ ድረስ ውሰዱ ስለተባለ ብቻ እንዲሁ ያንን የሚቀበለው አይሆንም" ያሉት ምንጩ "ነገሩን ቀስ ብለን እንየው በሚል ነበር የቆየው" ሲሉም አክለዋል። ቤልጂየም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የአውሮፓ ሕብረት ካውንስል ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ያንን መነሻ አድርጎ እርምጃ ይወስዳል ብሏል። "ርምጃው ምንድን ነው የሚለው ገና የሚታይ ነው የሚሆነው" ሲሉ የመረጃ ምንጫችን ነግረውናል።

ስለ አውሮጳ ኅብረት ርምጃ ምን ተባለ?

የአውሮጳ ኅብረት አቋሙን ዳግም እንዲያጤን የጠየቀው ኤምባሲው ኢትዮጵያውያን ዜጎች ከአውሮጳ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትን አሠራር በተመለከተ ከተሰጠው ውሳኔ ጋር በሚጣጣሙ ርምጃዎች ዙሪያ በሂደት ይመክራል ብሏል።

ወጣት ስደተተኞች በስደተኞች መቀበያ ጣቢያ አቅራቢያ
ወጣት ስደተተኞች በስደተኞች መቀበያ ጣቢያ አቅራቢያ ምስል Patrick Pleul/ZB/dpa/picture alliance

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ድዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የሕብረቱ ውሳኔ የማይጠቅም ውሳኔ ነው ሲሉ በ ቀድሞው ትዊተር - ኤክስ ጽፈዋል። ጉዳዩ በኢትዮጵያና አውሮፓ ሕብረት ግንኙነት ውስጥ አዋኪ ሊሆን እንደማይገባው ያስታወቁት ሚኒስትር ድኤታው ችግሩ በአፋጣኝ  ሊፈታ የሚገባው መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ እና የሕብረቱ ግንኙነት በተለይ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በግጭት ማቆም ስምምነት ከተቃጨ በኋላ መሻሻል ማሳየቱን ደጋግሞ ገልጻል።

የአውሮጳ ሕብረት ተልእኮ በኢትዮጵያ ከዚህ ስምምነት በኋላ በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያስደነገገው የትጥቅ ግጭትን ተከትሎ በተለይ መራዊ ከተማ ላይ በርካቶች የተቀጠፉበት ግድያ በነጻና ገለልተኛ ቡድን ተጣርቶ የወንጀሉ ፈጻሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ መጠየቁ ይታወሳል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ