1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፖለቲከኛ በቴ ህልፈትና የቤተሰቡ እጣ ፈንታ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 11 2016

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የነበሩት ፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ በአሰቃቂ ሁኔታ በትውልድ አካባቢያቸው መቂ ከተማ ተገድለው ከተገኙ 11 ቀናት አልፈዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥም በርካቶችን ያስቆጣው የፖለቲከኛው ግድያ በርካታ ሁነቶችን አስተናግዷል።

https://p.dw.com/p/4ezRl
ፎቶ፤ በቴ ዑርጌሳ
በቅርቡ ለተገደሉት ለአቶ በቴ ዑርጌሳ ፍትህ እየተጠየቀ ነው። ፎቶ፤ በቴ ዑርጌሳ ምስል Private

የአቶ በቴ ቤተሰብ እጣ ፈንታ

 

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የነበሩት ፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ በአሰቃቂ ሁኔታ በትውልድ አካባቢያቸው መቂ ከተማ ተገድለው ከተገኙ 11 ቀናት አልፈዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥም በርካቶችን ያስቆጣው የፖለቲከኛው ግድያ በርካታ ሁነቶችን አስተናግዷል። የሰብኣዊ መብት እና በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ግድያውን አውግዘው ሀቀኛና ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል። ከዚህ ጎን ለጎን ግን አቶ በቴ በሕይወት እያሉ እንደማንኛውም ሰው የራሳቸው የሆነ ቤተሰብ ያፈሩና የሚያስተዳድሩ እንደመሆናቸው፤ ቤተሰቦቻቸው እንዲረዱና እንዲጽናኑ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅስቀሳ ያደረጉም ጥቂት አይደሉም።

የአራት ልጆች አባት፤ አቶ በቴ ዑርጌሳ

አቶ በቴ የአራት ልጆች (ሦስት ሴት እና አንድ ወንጅ) አባት ነበሩ። የመጀመሪያ ልጃቸው 13 ዓመቱ ሲሆን የመጨረሻዋ አራት ዓመቷ ነው። አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የሟቹ ፖለቲከኛ ባለቤት ወ/ሮ ስንታየሁ አንበሴ አቶ በቴን ለልጆቻቸው መልካም አባት የነበረ ይሏቸውል።

«በቴ ከአባትም አባት ነው። ውጪ እንደምታየው ነው። አስተዋይና መልካም አባት ነው። ለልጆቹና ለቤቱም መልካም አባት ነበር» ነው ያሉት።

ወ/ሮ ስንታየሁ አክለውም፤ አቶ በቴ በትውልድ አካባቢቸው መቂ ተመላልሰው የግብርና ሥራን በመሥራት አዲስ አበባ ዙሪያ ቤት ተከራይተው እንደሚኖሩና በዚያው ቤተሰባቸውን ሲያስተዳድሩ እንደነበር አስረድተዋል። ከፖለቲከኛው ህልፈት በኋላ በርካቶች ከማጽናናት ጀምረው አጠገባቸው መቆማቸውን በማንሳትም የሚገኙበትን ሁኔታ ሲገልጹ፤ «ድሮም ኪራ ቤት ውስጥ ነን አሁንም ኪራይ ቤት ውስጥ ነን ያለነው። በግብርና ነበር ስንተዳደር የነበረው። ፈጣሪ የፈቀደውን ነው የምንኖረው። ሰው የወደደውን ቢደርግልን መልካም ነው። አሁንም በርካቶች ከጎናችን ቆመው አጽናንተውናል። ፈጣሪ ይስጥልን ነው የምለው» ብለዋል።

የባለቤታቸውን ግድያ ያልታሰበና በምንም መልኩ ያልጠበቅነው ያሉት ወይዘሮዋ፤ «በምንም መልኩ አልጠበቅንም።፡ ድንገት ነው የሆነው። ማን እንዳደረገም አናውቅም» በማለት ፍትህ እንደሚሹ አስረድተዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አርማ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አርማ

የአቶ በቴ ግድያ እና ውዝግቦቹ

የፖለቲከኛውን ህልፈት ተከትሎ በርካታ ውዝግቦች ላለፉት አስር ቀናት ተስተጋብተዋል። በዚህ ዙሪያ ይደረጋል ከተባሉ ዘርፈ ብዙ ምርመራዎች ውስጥ እስካሁን አንዱም ይፋ አልተደረገም፡፡ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በዚህ ግድያ የተናጠል ምርመራ እንደሚደርጉ ካሳወቁ ተቋማት ተጠቃሽ ናቸው። ከፖለቲከኛው ግድያ በኋላ አስከሬኑ ከመቀበሩ አስቀድሞ በመቂ ሆስፒታል በተደረገው ምርመራ ቦታው ላይ የነበሩ አንድ የህክምና ባለሙያ አየሁ ያሉትን ለዶቼ ቬለ ሲያስረዱ፤ «ብዙ ቁስል በአካላቸው ላይ ተመልክተናል። እነዚህ ቁስሎች የጥይት ቁስል ይመስላሊ። እኔ እንደተመለከትኩት ወገቡ ላይ ሦስት ቁስሎች አሉ። እግር በተለይ ጭኖቹ አካባቢም ሁለት ቁስል እና በጎኑ፣ በጀርባው እንዲሁም በሆዱ ላይም ቁስሎችን ተመልክተናል። ጭንቅላቱ ላይም አምስት ቁስሎች አሉ» ማለት ተመለከትኩ ያሉትን ዘርዝረዋል። ፡

የፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳን ግድያ ተከትሎ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ገለልተኛ የግድያ ምርመራ እንደሚደረግ በማግስቱ ባወጣው መግለጫ ማሳወቁ አይዘነጋም። ይህንኑ መግለጫ ተከትሎም የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ 13 ተጠርጣራችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አሳውቋል። ዶቼ ቬለ ከምንጮቹ እንዳረጋገጠው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ የሟች ፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ እህት እና ወንድም የሚገኙ ሲሆን እህታቸው ለፖሊስ ቃል ሰጥተው ተሰናብተዋል። ወንድማቸው ግን አሁንም ድረስ በቁጥጥር ስር ይገኛሉ።  

ማክሰኞ ሚያዚያ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ካደሩበት ማረፊያ ተወስደው መገደላቸው የተነገረው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የነበሩት ፖለቲከኛ ቤቴ ዑርጌሳ ሐሙስ ሚያዚያ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በትውልድ አካባቢያቸው መቂ መቀበራቸው ይታወሳል።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ