1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰማይ ደሴት ተመራማሪው ኢትዮጵያዊ ምሁር

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 24 2016

ተራራማ ምድር የተወለደው የያኔው ብላቴና ደሳለኝ እንደምን የአፍሪቃን ማማዎች አዳረሰ ? እንደምንስ የሰማይ ደሴት ተመራማሪ ሊሆን ቻለ ? በምርምሩስ ምን ላይ ደርሶ ይሆን ?

https://p.dw.com/p/4fR2d
Dr. Desalegn Chala
ምስል privat

ትላልቅ የአፍሪቃ ተራሮችን ያደረሱ ኢትዮጵያዊ ምሁር የህይወት መስመር

 

የሰማይ ደሴት ተመራማሪው

ትውልድ እና ዕድገት

አፍሪቃ ውስጥ የሚገኙ ትልልቅ ተራሮችን አንዴ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ጊዜያት  ተመላልሰው በመውጣት የስነ ምህዳር ምርምር ያደረጉ የዕለቱ እንግዳችን  ዶ/ር ደሳለኝ ጫላ ይባላሉ ። ነዋሪነታቸው በሀገረ ኖርዌይ ኦስሎ ውስጥ ነው ። ዶ/ር ደሳለኝ ቀደም ሲል ወደ አውሮጳ ያመሩት የሁለተኛ ዲግሪ መርኃ ግብር ትምህርታቸውን ለማጥናት እንደሆነ ነበር የነገሩን ። ነገር ግን  ትምህርታቸውን በሁለተኛ ወይም በማስተርስ ዲግር አልገደቡም ፤ ይልቁኑ ሶስተኛውን የፒኤች ዲ ዲግሪ መርኃ ግብር በዚያው ገፉበት እንጂ ። 

ትውልድ እና ዕድገታቸው ኦሮሚያ ክልል በተራራማው  የምዕራብ  ሸዋ  ሶዶ አካባቢ ነው ። ዶ/ር ደሳለኝ  የትውልድ መንደራቸውን እና ልጅነታቸውን ለአፍታ መልስ ብለው ያስታወሱትን አካፍለውናል ።
«የተወለድኩት ምዕራብ ሸዋ ሶዶ የሚባል አካባቢ ነው። ሶዶ በጣም ሰፊ ነው ፤ ከቱለማ 40 ወረዳዎች ወደ ስድስቱ የሚገኙት እዚያ ነው። አካባቢው በጣም ተራራማ ነው።»
ተራራማ ምድር የተወለደው የያኔው ብላቴና ደሳለኝ እንደምን የአፍሪቃን ማማዎች አዳረሰ ? እንደምንስ የሰማይ ደሴት ተመራማሪ ሆነ ? በምርምሩ ምን ላይ ደርሶስ ይሆን ?  የዚህኛውን የታሪክ ክፍል ዘግየት ብለን እንመለስበታለን፤ አድማጮቻችን ።

ዶ/ር ደሳለኝ ጫላ
ዶ/ር ደሳለኝ ጫላ ትውልድ እና ዕድገታቸው ኦሮሚያ ክልል በተራራማው  የምዕራብ  ሸዋ  ሶዶ አካባቢ ነውምስል privat

 በበረዶ ዘመን በባሌ ተራራ ሰዎች እንደኖሩ በጥናት ተረጋገጠ


ከትውልድ መንደራቸው የጀመረው የትምህርት ዕድገታቸው እንዲሁ በቀላሉ የታለፈ አልነበረም ፤ ለዶ/ር ደሳለኝ ። ከሩቁ የገጠር ክፍል ይነሳና መዲናዪቱ አዲስ አበባን አቋርጦ ባህር ይሻገራል። 

የዶ/ር ደሳለኝ የትምህርት መስመር 
«ኤሌመንተሪ እዚያ ነው የተማርኩት ፤ ሰባት እና ስምንስት ባንቱ የምትባል ከተማ ፣ ከዚያም ዘጠነኛ ክፍል ቱሉ ቦሎ ከዚያ በኋላ ነው ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት ፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን መነን ነው የተማርኩት ፤ ከዚያ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ በባዮሎጂ ፤ሁለተኛ ዲግሪ በእጽዋት ሳይንስ ሰርቻለሁ ፤ ከዚያ ወደ ሆላንድ ሂጄ በሳተላይት ምስል ትንተና የሁለተኛ ዲግሪ መስራት ችያለሁ» 
ከገጠሪቱ የደቡብ ሸዋ የጀመረው ጉዞ ኔዘርላንድስ ደርሶ አልቆመም ። ተጨማሪ ትምህርት፣ ተጨማሪ ዕውቀት የሚጠይቅ እና አንድ እርምጃ ወደ ፊት የሚያራምድ ጉዞ ከደቾች ምድር ወደ ሰሜን ጠርዝ የስካንዴቪያኑ ምድር አመራ ። መዳረሻውም መዲናዪቱ ኦስሎ ነበር። እንግዳችንን ለዛሬው የእንግድነት ግብዣ ያስጠራቸው እና ከበርካታ የምርምር መስኮች አንዱ ወደ ሆነው የተራሮች ስነ ምህዳር  የምርምር መስክ የመሳተፍ እድልን አስገኘላቸው። 

ዶ/ር ደሳለኝ ጫላ
ከገጠሪቱ የደቡብ ሸዋ የጀመረው ጉዞ ኔዘርላንድስ ደርሶ አልቆመም ። ተጨማሪ ትምህርት፣ ተጨማሪ ዕውቀት የሚጠይቅ እና አንድ እርምጃ ወደ ፊት የሚያራምድ ጉዞ ከደቾች ምድር ወደ ሰሜን ጠርዝ የስካንዴቪያኑ ምድር አምርቷል ። ምስል privat

 « ወደ ኦስሎ ዩኒቨርሲቲ ከመጣሁ በኋላ ነው የተራራ ላይ ምርምር የተጀመረው ፤ የተራሮች ስነ ምህዳር ላይ ሶስተኛ ዲግሪዬን የሰራሁት በፈረንጆቹ 2006 የፒኤች ዲ ዲግሪዬን መያዝ ችያለሁ፤ እስካሁኔም በዚያው እየተመራመርኩ እገኛለሁ »
ዶ/ር ደሳለኝ በኖርዌይ ሕይወት ሰምሮላቸዋል፤ ትዳር መስርተዋል፤ የሁለት ልጆችም አባት ናቸው ። ይህ አፍሪቃን በሚያዳርሰው የተራሮች ጉዟቸው አጋዥ ሳይሆናቸው አልቀረም ።

 የኪሊማንጃሮ ተራራ በሰደድ እሳት መያያዝ እና የአካባቢው ስነምህዳር


ስለረዛዥም ተራሮች ጉዞ ሲነሳ ሰዎች አንድም ለጉብኝት አልያም ለስፖርታዊ ጉዞ ለረዥም ጊዜ አስቀድሞ በሚያዙ ዕቅዶች የሚሸፈኑ ፤ አስጎብኚዎችን ሊያሳትፍ በሚችል ሁኔታ ውስጥ ያልፋል። ሂደቱ ፈተና የበዛበት ይሆንና ህይወትን ለአደጋ የሚያጋልጥበት ሁኔታ ሁሉ  ሊፈጠር ይችላል። ተራራ ለተራራ እየባጠጡ የምርምር ስራዎችን ማከናወን ሲታከልበት ደግሞ የቆይታ ጊዜ ማራዘሙ አይቀርምና ቀላል አይሆንም። ለዶ/ር ደሳለኝ የትውልድ መንደራቸው ተራራማ መሆን ነገሮችን አቅልሎቸው ይሆን ?

ተራሮችን ለመመራመር ምክንያት የሆናቸው ምን ይሆን ?
 « ይመስለኛል ፤ ዕድገቴ ይመስለኛል ፤ የኛ ቤት ራሱ ከባህር በላይ ሶስት ሺ ሜትር ከፍታ በላይ ነው የሚገኘው ። እንዳልኩህ ቅርብ የሚመስሉ ቦታዎች ሁሉ ሩቅ ናቸው ለምሳሌ ቱሉ ቦሎ ለመድረስ በእግር ቢያንስ ስምንት ሰዓት መጓዝ ይጠበቅብናል፤ ግን ተራራ ላይ ቁች ብዬ ማታማታ መኪና ሲንቀሳቀስ አያለሁ ፤ ያ በብዙ መልኩ በእኔ ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ ይመስለኛል። » 
በኬንያ እና በታንዛኒያ ድንበር መካከል የተዘረጋው በአፍሪካ ውስጥ ትልቁ ተራራ የኪሊማንጃሮ ተራራ ሲሆን 5,895 ሜትር ከፍታ አለው። የተራራው አናት ላይ ደርሰው ለመመለሰ በጥቅሉ እስከ አስር ቀን ሊወስድ እንደሚችል ነው የሚነገረው ።

ዶ/ር ደሳለኝ ጫላ
በኬንያ እና በታንዛኒያ ድንበር መካከል የተዘረጋው በአፍሪካ ውስጥ ትልቁ ተራራ የኪሊማንጃሮ ተራራ ሲሆን 5,895 ሜትር ከፍታ አለው።ምስል privat

 ከኪሊማንጃሮ ተራራ በተጨማሪ ሌሎች በአህጉሪቱ በትልቅነታቸው የሚታወቁ ተራሮች ዘመን ተሻጋሪ እና አስደናቂ የቱሪዝም መስህብ ሆነው መቆየት የቻሉም ናቸው ። ዶ/ር ደሳለኝ እንደሚሉት በየተራሮቹ የሚታዩ ግግር በረዶዎች ዘመን ተሻጋሪ ገጽታቸውም ሆነውላቸዋል።

 
« በተለይ ሩዌንዞሪ የሚባለው ቦታ ፤ የኬንያ ተራራ ፣ የኪሊማንጃሮ ተራራ ፣ እስካሁን ድረስ ያልቀለጡ በረዶዎች ያሉባቸው ተራሮች ናቸው። በተለይ ሩዌንዞሪ ያለው የበረዶ ግግር እንዴት ያምራል መሰለህ ፤ በረዶ ግግሩ ላይ ቆመህ ወደ ታች ስትመለከተ ደመና ነው የሚታይህ ልክ ከአውሮፕላን ላይ ሆነህ እንደምትመለከተው።»
በጥናት እና ምርምሩ የተሳተፉ ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያውያን ምሁራን እንዳሉዶ/ር ደሳለኝ ከዶይቼ ቬለ ጋር በነበራቸው ቆይታ አጋርተውናል።

በሰሜን ተራሮች የተነሳው ቃጠሎ አሁንም አልጠፋም

 

ስለተራሮች እና ስነምህዳሮቻቸው ሲነሳ የአጠቃላይ አፍሪቃ ረዛዥም ተራሮችን 80 በመቶ የምትይዘው ኢትዮጵያ እንደሆነች ነው የሚነገረው ። በዚህም ነው ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪቃ ማማ ተብላ እስከመጠራትም የደረሰችው ። እነዚህን በተለይ ከ3500 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ከፍታ ያላቸውን ተራሮች ሌሎች የምስራቅ አፍሪቃ ሃገራት የተጠቀሙበትን ያህል ለቱሪዝም መዳረሻነት ጥቅም ላይ ውለዋል ለማለት አያስደፍርም ።

ዶ/ር ደሳለኝ ጫላ
ተለይ ሩዌንዞሪ የሚባለው ቦታ ፤ የኬንያ ተራራ ፣ የኪሊማንጃሮ ተራራ ፣ እስካሁን ድረስ ያልቀለጡ በረዶዎች ያሉባቸው ተራሮች ናቸው።ምስል privat

በቅርቡ  የተባበሩት መንግሥታት፤ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበው የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ባርክን ጨምሮ ቀደም ሲል የተመዘገበው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርኮች በተፈጥሯቸውም ሆነ በውስጣቸው በያዟቸው ብዝሃ ህይወት እና ስነ ምህዳር በእርግጥ ለጎብኚዎች በእጅጉ አመቺ ናቸው ። ችግሩ የሚመነጨው ግን እነዚህን እጹብ ድንቅ አካባቢዎች ለተቀረው ዓለም የማስተዋወቅ እና ተገቢውን ጥበቃ እና እንክብካቤ የማድረጉ ነገር በሚገባው ልክ ትኩረት ሳያገኝ ሲቀር ነው ። እንደ ዶ/ር ደሳለኝ ያሉ በመስኩ ስነምህዳሮችን ለይተው  የመረመሩቱ ደግሞ ኢትዮጵያ የተለየ የስነምህዳር እና የተፈጥሮ አካባቢ እንዳላት ለማሳየት ተወልደው ያደጉበትን ቀዬ በትንሽ ጥናት ማስደገፍ ብቻውን በቂ ሊሆን ይችላል። 
ታምራት ዲንሳ 

ነጋሽ መሐመድ