1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕፃናት ልምሻ እና ወባ በሽታ በትግራይ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 22 2016

በትግራይ የሕፃናት ልምሻ ወይም ፖልዮ እና ወባ በሽታዎች በወረርሽኝ ደረጃ መታየታቸው ተገለፀ። ባለፉት 8 ወራት ከ190 ሺህ በላይ ህዝብ በትግራይ በወባ በሽታ የተያዘ ሲሆን የሕፃናት ልምሻ ወይም ፖልዮ በሽታም በአንዳንድ ወረዳዎች በወረርሽኝ ደረጃ እየታየ መሆኑ የትግራይ ጤና ቢሮ ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4fLu7
Äthiopien Gesundheitsstation in Tigray
ምስል Million Hailesilassie/DW

የሕፃናት ልምሻ እና ወባ በሽታ በትግራይ

በትግራይ የሕፃናት ልምሻ ወይም ፖልዮ እና ወባ በሽታዎች በወረርሽኝ ደረጃ መታየታቸው ተገለፀ። ባለፉት 8 ወራት ከ190 ሺህ በላይ ህዝብ በትግራይ በወባ በሽታ የተያዘ ሲሆን የሕፃናት ልምሻ ወይም ፖልዮ በሽታም በአንዳንድ ወረዳዎች በወረርሽኝ ደረጃ እየታየ መሆኑ የትግራይ ጤና ቢሮ ገልጿል። ይህ ለመከላከል 2 ሚልዮን ህፃናት ለመከተብ ያለመ ፀረ ፖልዮ ዘመቻ ተጀምሯል።

የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ እንደሚለው፥  የወባ በሽታ ስርጭት በተለይም ከጦርነቱ በኃላ በከፍተኛ መጠን የጨመረ ሲሆን ባለፈው ዓመት ብቻ 230 ሺህ ህዝብ በትግራይ በወባ መለከፉ፥ በያዝነው ዓመት 8 ወራት ብቻ ደግሞ 190 ሺህ ሰው በክልሉ ለወባ በሽታ መጋለጡ ይገልፃል። ለዚህ የወባ ጨምሮ የተለያዩ በሽታዎች መዛመት እንዲሁም በወረርሽኝ መልክ መታየት ምክንያት፥ ጦርነቱ ተከትሎ የክልሉ የጤና ስርዓት መፍረሱ፣ የግብአቶች እና ተደራሽነት እጥረቶች መሆናቸው ተነግሯል። 

በትግራይ ጤና ቢሮ የወባ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ሐላፊ አቶ ገብረመድህን ክንፉ "በሽታው እንዳይሰራጭ አስፈላጊ የተባሉ ተጨማሪ መድሃኒቶች እጥረት ስላለ ከጤና ሚኒስቴር እና ሌሎች የሚመለከታቸው ይጠበቃል። ዛንዜራ፣ ለኬሚካል ርጭት የሚጠቅሙ ግብአቶች ለማፈላለግ ነው ታቅዶ ያለው" ይላሉ። ከወባ ውጭ የልጅነት ልምሻ ወይም ፖልዮ በሽታም እንዲሁ በትግራይ ክልል ጨርጨር ወረዳ በወረርሽኝ መልክ መታየቱ ተገልጿል። የልጅነት ልምሻ ወይም ፖልዮ በክልሉ የመንሰራፊት ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑ ተከትሎ የትግራይ ጤና ቢሮ እና አጋር የተባሉ አካላት በጋራ የፖልዮ ክትባት ዘመቻ በትግራይ መሰጠት ተጀምሯል። በዚህ የክትባት ዘመቻ ከሁለት ሚልዮን በላይ የትግራይ ህፃናት ለመከተብ መታቀዱም የትግራይ ጤና ቢሮ ሐላፊ ዶክተር አማኑኤል ሐይለ በዘመቻው መባቻ ተናግረዋል። 

ፎቶ ማህደር፤ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ ሁኔታ
ፎቶ ማህደር፤ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ ሁኔታ ምስል Ed Ram/Getty Images

ዶክተር አማኑኤል "የአሁኑ ዘመቻ ከሌላው ለየት የሚያደርገው፥ እንዲከተቡ ያቀድነው የህፃናት ቁጥር በከፍተኛ መጠን ነው መፈፀም ያለበት። የፖልዮ ማጥፋት ዘመቻ ውጤታማ ሊሆን ከተፈለገ ሰባ እና ሰማንያ ከመቶ ህፃናት ሳይሆን ከ95 በመቶ በላይ መክተብ አለብን። ከአስር ዓመት በታች የሆኑ ሁለት ሚልዮን ገደማ ህፃናት የፖልዮ ክትባት ለመከተብ ነው ያቀድነው። ከነዚህ መካከል ከ95 በመቶ በላይ ከከተብን ነው ዘመቻው ውጤታማ ሆነ የምንለው" ብለዋል። ከጦርነቱ በኃላ በትግራይ የጤና አገልግሎት መሻሻሎች ቢታይበትም አሁንም የግብአት እጥረት እና የባለሙያዎች ፍልሰታ አሳሳቢ ነው።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ